አክስዮን ማህበሮች ብሔር አላቸውን?

አእምሮአችን የተለያዩ ሃሣቦች ይመላለሱበታል፤ ለምን ቢባል የአንድ ሰው ትልቅነት የሚለካው በምናቡ በሚያብሰለስላቸው ሀሣቦችና በሀሣብ አፍላቂነቱ ነውና፡፡ ይህን ሁሉ የመላችሁ አንድ መልስ ላገኝለት ያልቻልኩት ጥያቄ በአእምሮዬ እየተመላለሰ ስላስቸገረኝ ነው፡፡ ጥያቄውም፡- “አክሲዮን ማህበሮች ብሔር አላቸውን?፣ ማዳላትስ ይችላሉን?” የሚለው ነው፡፡ እንደምታውቁት አክስዮን ማህበሮች ሰዎች ትላልቅ ኢንቨስትመንት በሚፈልጉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ለመሳተፍ ገንዘባቸውና ንብረታቸውን በማዋጣት ትርፍ ለማግኘት የሚያቋቁማቸው የንግድ ተቋማት ናቸው፡፡ አክስዮን ማህበሮች፣ ግዑዛን የህግ ሰውነት ያላቸው አርቴፊሻል ተቋማት ናቸው፡፡ የሚመሰረቱትም መስራቾች ተብለው በሚታወቁ የተፈጥሮ ሰዎች ነው፡፡

ይህን ለማንሳት የፈለኩት፣ በዚህ ሳምንት ካጋጠመኝ ለማመን የሚከብድ ገጠመኝ ላካፍላችሁ ስለወደድኩኝ ነው፡፡ ጉዳዩ የተፈጠረው፣ ሥራ በምፈልግበት ስዓት ኣንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ የሥራ ማስታወቂያ ያወጣና መስፈርቱን አሟላለሁ ብዬ ስላመንኩኝ አመለክታለሁ፡፡ ካመለከትኩ ከአንድ ወር በኋላ ከጓደኞቼ ስንጨዋወት፣ ለፈተና መጥራቱን ሰማሁኝና ከጓደኞቼ ተመሣሣይ ውጤት ስለነበረኝ ተሳስተው ይሆናል ያልጠሩኝ ብዬ በማሰብ ብሔራዊ ጋር ወደሚገኘው ዋናው መስሪያ ቤታቸው ሄጄ ጠየኩኝ፡፡ 13ኛ ፎቅ በሚገኘው የሰው ሀብት አስተዳደር ቢሮ ገብቼ አንድ ረዘም ያለ ጠይም ወጣት ያልተጠራሁት ስልኬ አስቸግሯቸው እንደሆነ ጠየኩት፤ እሱም ስሜን ጠየቀኝ እኔም አዲስአለም ደስታ ስል ነገርኩት፡፡ እሱም መልሶ አዲስ አለም ጉታ ነህ? አለኝ፡፡ አለመሆኔን ነግሬው ትክክለኛ ስሜን ደግሜ ነገርኩት፡፡ እሱም “በዚህ ስም አልጠራንም” አለኝ፡፡ እኔም በ3.29 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረቅኩኝ፣ 6 ቋንቋ መናገር የምችል እና ሌሎች የምስክር ወረቀቶች እያሉኝ ሳልጠራ እንዴት 2.8 ያመጣ ተጠራ ብዬ ጠየኩኝ፤ መልሼም እኔን ላለመጥራት እንዲወስኑ ያደረጋቸው መስፈርታቸው እንዲነግረኝ ብጠይቀውም የድርጅቱ አሰራር አይፈቅድም ብሎ ነበር የመለሰልኝ፡፡ አለቃውን ላናግር ወሰንኩኝና የመድህን ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ለማናገር በማሰብ ወደ 15ኛ ፎቅ ወጣሁኝ፡፡ ሥራ አስኪያጅም ስላልነበሩ ፀሐፊዋ ደውላ የሰው ሀብት አስተዳደር ኦፊሰር እንዳናግር ወደ 13ኛ ፎቅ መራችኝ፡፡ ፀሐፊያቸው ምክንያቴን ጠይቃ ገብታ ስታናግራቸው ሊያገኙኝ ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ነገረችኝ፡፡ ወደሥራ ቦታዬ ተመልሼ ለሥራ ባልደረቦቼ ያጋጠመኝን ሳጫውታቸው እውነታውን አረዱኝ፡፡ የትኛው ባንክና መድህን ድርጅት የየትኛውን ብሔር እንደሚቀጥር፣ ፈተና ሳትቀርብ ስም ብቻ አይተው እንደሚመርጡ፣ እና በማስታወቂያው መስፈርት ያልነበረ ነገር ያልፈለጉትን ሰው ለማግለል የማይገናኝ ነገር መስፈርት እንደሚያደርጉ ነገሩኝ፡፡ እኔ ያመለከትኩበት  የመድህን ኩባንያም ለአንድ ብሔር ተወላጆች ቅድሚያ እንደሚሰጥ በአዘኔታ ከንፈራቸውን እየመጠጡ አስገነዘቡኝ፡፡

አንድ አገር ሆነን፣ በብቃትና ክህሎት ማመን ሲገባን፣ ለምን በጐሣና በብሔር ታጥረን በጭፍን ህሊናችን የማይቀበለውን ሥራ እንሠራለን፡፡ ለምን ትልቁን ስዕል አናይም፡፡ ለምን ቀድሞ ኢትዮጵያዊነታችን ትዝ አይለንም? እንዴት ያስተሣሰረንን ያብሮነት ገመዳችን እንዘነጋዋለን?

                                                                                                            ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s