የዲፕሎማሲ ሠራተኞች አስተዳደር የሚመለከቱ በስራ ላይ ያሉ አጠቃላይ ሕጎች እና አተገባበራቸው የዳሰሳ ፅሑፍ
አዘጋጅ፡- አዲስአለም ደስታ(LLB)
ነሓሤ 11 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
መግብያ
በጥቂት የዉጭ ግንኙነት አጀንዳዎችና በዉስን ተዋንያን ታጥሮ የነበረው ጥንታዊ የዲፕሎማሲ አሰራር በሂደት ዳብሮና ተለዉጦ የዘመኑ ዓለም አቀፍ ግንኙነት የደረሰባቸው ስፋትና ጥልቀት ያላቸው ዉስብስብ የዲፕሎማሲ ስራዎች በርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተዋንያን በመከናወን ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ከሽብርተኝነት፣ ከሕገወጥ የሰዎችና የዕቃዎች ዝዉዉር፣ ከአየር ንብረት መዛባት፣ ከሰብአዊ መብቶች እንዲሁም ከሌሎች በርካታ ኢኮኖምያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ዲፕሎማስያዊ ሥራዎች በተለያዩ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ በመንግስታት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በዜጎችና በፓርላማዎች ወ.ዘ.ተ. የሚከናወኑ ናቸው።
በዚህ ረገድ የበርካታ አገሮች ልምድና አሰራር እንደሚያመለክተው እነዚህ በሉዓላዊ መንግስታት አማካኝነት በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ የሚደረጉት የዉጭ ግንኙነት እንቅስቃሴዎች የየመንግስታቱን ብሔራዊ ጥቅሞች ማስከበርያ ግቦች ለማሳካት በሚያስችል መልኩ ከዉጭ ጉዳይ በተጨማሪ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍና ወጥነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ በመዘርጋት ግልጽ በሆነ የአሰራር ሥርዓት የሚመሩ ናቸው።
በአገራችንም የዉጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ለማስፈፀም ከዉጭ ጉዳይ በተጨማሪ ሌሎች የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 በተሰጣቸው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዉጭ ግንኙነት እንቅስቃሴው ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ይሁንና ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዘመናት ሲያከናዉናቸው የቆየዉን የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት ሥራዎች ግልጽ፣ ቀልጣፋና ዉጤታማ በሆነ መንገድ ለመምራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አስተባብሮና አቀናጅቶ በተሻለ ሁኔታ ለመስራት የሚያስችል፣ የሌሎች አገራት ጠቃሚ ልምድና ተሞክሮ፣ እንዲሁም ያለንበትን የዓለም አቀፍ ፣ አህጉራዊና አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት የሚያስገባ ዘመናዊ የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት ለመገንባት የሚያችል ወጥነት ያለው የሕግ ማዕቀፍና የተጠናከረ ተቋማዊ የአሰራር ሥርዓት ዘርግቶ ለመንቀሳቀስ አልተቻለዉም።
ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ግልጽ፣ ቀልጣፋና ዉጤታማ የሆነ ተቋማዊ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት፣ አቅሙ፣ ብቃቱና ክህሎቱ የዳበረ ቁርጠኛ የዲፕሎማሲ ሠራዊት ለማፍራት፣ ዘመናዊና ሙያዊ የዲፕሎማሲ አገልግሎት(Career Diplomatic Service) ለመገንባት፣ እንዲሁም አግባብነት ያላቸው ባለድርሻ አካላትን አስተባብሮና አቀናጅቶ ለማንቀሳቀስ፣ በድምሩ ዉጤቱም አገራዊ ተልዕኮን በተሻለ ሁኔታ ለማሳካት እንዲያስችል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ እንደፀደቀ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ካዘጋጀው መግለጫ መረዳት ይቻላል።
በስራ ላይ ያሉ አጠቃላይ ሕጎች
አሁን በስራ ላይ ያሉት በዲፕሎማሲ አገልግሎት ዙርያ ላይ ተፈፃሚነት ያላቸው ሕጎች በዋነኝነት የኢትዮጵያ ፌዳራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ- መንግስት፣ የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 790/2005 እና የፌደራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/1999 ናቸው።
ሕገ-መንግስቱ ሁሉም ኢትዮጵያዉያን የሀገሪቱ የተጠራቀመ ዕውቀትና ሀብት ተጠቃሚዎች የሚሆኑበትን መንገድ የመቀየስ፣ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች በማሻሻል እኩል ዕድል እንዲኖራቸው የማድረግ፣ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታ እንዳለበት ያስቀምጣል። በተጨማሪም፣ የሠራተኛዉን ህዝብ ጤንነት፣ ደህንነትና የኑሮ ደረጃ ለመጠበቅ መንግስት መጣር እንዳለበት ሕገ-መንግስቱ ይደነግጋል[1]። ሕገ-መንግስት አጠቃላይ ድንጋጌ እንደመሆኑ ዝርዘሩ በአብዛኛዉን ግዜ የሚወሰነው በአዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ነው። በተያዘው ርእሰ ጉዳይ ሕገ-መንግስቱ ለማስፈፀምና ዝርዝር ጉዳይ ለመወሰን የወጡት የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 790/2005 እና የፌደራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/1999 ናቸው። የዚህ የዳሰሳ ፅሑፍ ዓላማ፣ የአዋጁ ላለመተግበር በተወሰነ መልኩ የአዋጁ ይዘት በተገቢው አለማወቅ አንድ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል የዲፕሎማሲ ሠራተኞች አስተዳደር የሚመለከቱ በስራ ላይ ያሉ አጠቃላይ ሕጎች በተለይም በዉጭ ግንኙነት አዋጁ ያሉትን ክፍተቶች ማሳየት እና በአተገባበራቸው ላይ የሚታዩ ከአዋጁ ይዘት አለመጣጣም በማሳየት ለሚመለከታቸው አካላት ጠቃሚ የሆነ ግብአት መስጠት ነው።
ዲፕሎማት ማን ነው?
ዲፕሎማት ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ በተዘዋዋሪ መልክ መልስ የሚሰጠው “የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 790/2005 ነው። ትርጓሜው እየተመዘዘ የሚወጣ(Derivative definition) የሚባል ዓይነት ነው። ይሄ ማለት ዲፕሎማት ማን ነው የሚለዉን ጥያቄ ለመመለስ በመጀመሪያ፣ የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት፣ የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት ሠራተኛ፣ እና የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ዘርፍ በጥንቃቄ ማንበብ ያስፈልጋል። በመጨረሻም የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኛ በሚለው የወል ስም ማን እና የትኞቹ የሥራ ክፍሎች እንደሚያካትት መለየት ይቻላል።[2]
የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኛ ማለት በዲፐሎማቲክ አገልግሎት ዘርፍ የሚሰራ ሠራተኛ ነው። በዲፐሎማቲክ አገልግሎት ዘርፍ የተካተቱት በሚኒስትሩና በሚስዮን የተዘረጉ የሚከተሉት የስራ ክፍሎች ያካትታል። እነሱም፡-
- የፖለቲካ ዲፕሎማሲ
- የኢኮኖሚና ቢዝነስ ዲፕሎማሲ
- የፐብሊክ ዲፕሎሲና ኮሚዉኒኬሽን
- የፕሮቶኮል የስራ ክፍል
- የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች
- የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች
- የቆንስላ አገልግሎት
- የጾታና ርቱዓዊ ተሳትፎ ጉዳዮች እና
- ሌሎች በሚኒስትሩ የሚወሰኑ ተዛማጅ የስራ ክፍሎች
የተጠቀሱት የስራ ክፍሎች ዝርዝር ሁሉን አቀፍ(Exhaustive List) ሳይሆን አማላካች(Illustrative) የሚባል አገላለፅ ነው። ከተዘረዘሩት ዉጭ ያሉት የስራ ክፍሎች በዲፐሎማቲክ አገልግሎት ዘርፍ ለማካተት ሁለት መሰናክል ሊያልፉ ይገባል። እነሱም፡-
- ተዛማጅነት እና
- የሚኒስትሩ ዉሳኔ ናቸው።
ስለዚህ በዝርዝሩ ዉስጥ ያልተካተቱት የስራ ክፍሎች በዲፐሎማቲክ አገልግሎት ዘርፍ ለመካተት የሚኒስትሩ ዉሳኔ ብቻዉን በቂ አይደለም። ሚኒስትሩ አንድ የስራ ክፍል የዲፐሎማቲክ አገልግሎት ዘርፍ ነው ብሎ ከመወሰኑ በፊት፣ ከተዘረዘሩት የስራ ክፍሎች ቢያንስ ከአንድ የስራ ክፍል ተዛማጅ መሆን አለበት። እዚህ ላይ ሁለት ምሳሌዎች መጥቀስ ተገቢ ነው። የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ ከወጣ በኃላ የተቋቋሙት የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል እና የፖሊሲ ምርምርና ትንተና ዲፓርትመንት በየትኛው ዘርፍ እንደሚካተቱ ማየት ይቻላል። የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አካል የነበረ እንዲሁም የተለያዩ የፖለቲካ ዉሳኔ የሚወሰንበት እንደመሆኑ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ዉስጥ ሊካተት ይችላል። በተመሳሳይ የፖሊሲ ምርምርና ትንተና ዲፓርትመንት በአሁኑ ሰአት እየሰጠው ያለዉን “የፖለቲካ ምክር አገልግሎት”(የፖሊሲ ክፍተት በመለየት የፖሊሲ አማራጭ ማቅረብ) እንዲሁም የተቋቋመበት ዓላማ በማየት ከዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል የሚያመሳስል ባህሪ አላቸው፤ እሱም ሁለቱም በተለያየ ዘርፍ ቢሆንም የምክረ ሀሳብ ያቀርባሉ። እንዲሁም በአገራት ሁለትዮሽ ግንኙነት ያተኮሩ ስራዎች ስለሚሰሩ በፖለቲካ ዲፕሎማሲ ዉስጥም ሊካተት ይችላል። የተዛማጅነት ጥያቄ መስፈርት ስለሚያሟሉ እና ሁለቱ የተቋቋሙትም በሚኒስትሩ ዉሳኔ[3] በመሆኑ በዲፐሎማቲክ አገልግሎት ዘርፍ የሚካተቱ ናቸው።
ዲፕሎማት ማነው የሚለዉን ጥያቄ ከተመለሰ በኃላ ተከትለው የሚመጡት ጥያቄዎች የአቀጣጠር መንገድ፣ ስለሙከራ ግዜ፣ የደረጃ እድገት፣ ስለምደባ፣ ጥሪና ዝዉውር፣ ደሞዝ፣ መከበር ስላለባቸው የስነ-ምግባር መርሆች፣ ከስራ ስለመሰናበት፣ የሚሰጡ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችና የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ ተፈፃሚ የሚሆንበት አገባብ እንደሚከተለው ቀርቧል። በመጨረሻም በአፈፃፀም የሚታዩ ክፍተቶችና መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች አስተያት ለመስጠት ተሞክሯል።
የአቀጣጠር መንገድ
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመንግስት መስሪያ ቤት እንደመሆኑ በመርህ ደረጃ ቅጥር የሚከናወንበት መንገድ ከአድልዎ የፀዳ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት መሆን አለበት። እነዚህ መስፈርቶች እንዲያሟላ ከተፈለገም እንደአስፈላጊነቱ ለህዝቡ ተደራሽ በሆኑ የመገናኛ አዉታሮች የስራ ማስታወቅያ መዉጣት አለበት። ይሄንን ታሳቢ በማድረግም የዉጭ ግንኙነት አዋጁ የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኛ ሆኖ ለመቀጠር የሚፈልግ በአዋጁ የተቀመጡትን መስፈርቶች ማሟላት ይኖርበታል። እነሱም፡-
- ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆን
- ለሕገ-መንግስቱ ታማኝ መሆን
- በማናቸዉም የትምህርት ዘርፍ ዕዉቅና ከተሰጠው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ማቅረብ
- የተስማሚነት ማረጋገጫ ማጣርያን ማለፍ
- ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በስተቀር የጤንነት ማረጋገጫ የህክምና ምርመራ ማለፍ
- ዕድሜው ቢያንስ 21 ዓመት የሞላው
- ሚኒስቴሩ የሚያወጣቸዉን የመግብያ ፈተናዎች ማለፍ
- ከወንጀል ነፃ መሆኑን የሚያረጋግጥ የፖሊስ ማስረጃ ማቅረብ እና
- የዉጭ አገር ዜግነት ያላት የትዳር ጓደኛ ካለው ሚኒስቴሩን ማሳወቅ ናቸው።[4]
በተጨማሪ ከላይ የተዘረዘሩ መስፈርቶች እንደተጠበቁ ሆኖው የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኛ ምልመላ ዕዉቀትና ችሎታን መሠረት ባደረገ ግልጽ ዉድድር መሠረት እንደሚፈፀም ይደነግጋል።[5] በዚህ መሰረት አንድ ሰው ቋሚ የዲፐሎማቲክ አገልግሎት ዘርፍ ሰራተኛ ለመሆን የሚከተሉትን ሂደቶች ማለፍ አለበት፡-
- የተቀመጡትን መስፈርቶች ማሟላት
- ሚኒስቴሩ የሚያወጣቸዉን የመግብያ ፈተናዎች ማለፍ
- የተስማሚነት ምዘና ማለፍ
- የሙከራ ግዜዉን መጨረስ እና
- የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ማለፍ ናቸው።
ተስማሚነት ማለት የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት ዕጩ ተቀጣሪ ቅድመ-ቅጥር ወይም ቋሚ የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት ሠራተኛ ድህረ-ቅጥር ማንነት መረጃ በተመለከተ እንደሁኔታው ለመቀጠር ወይም በቅጥር ለመቀጠል ይችል እንደሆነ ብቃቱ ወይም ተገቢነቱ የሚረጋገጥበት ነው። የተቀጣሪ ተስማሚነት የማጣራት ስራ ዋናው ዓላማዉ ተቀጣሪው የተደበቀ ማንነት አለመኖሩን፣ በተለያዩ የዉስጥና የዉጭ ኃይሎች ጫና ስር ያልወደቀ፣ ለተለያዩ ጎጂ ሱሶችና ባህሪያት ያልተጋለጠ መሆኑንና በስራው አጋጣሚ የሚያያቸዉን፣ የሚሰማቸዉን የሚይዛቸዉንና የሚሰራባቸዉን ሚስጥራዊ መረጃዎች በአግባቡ መያዝ የሚችል መሆኑን ለማጣራት እና በአጠቃላይ የሚሰጠዉን አገራዊ ተልዕኮ በታማኝነት ሊወጣ የሚችል በሆንን አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሚሰራ የማረጋገጥ ስራ ነው።[6]
የቅጥር መስፈርቶቹ ተመሳሳይነት ያላቸው ቢሆንም የአስተዳደርና የቴክኒክ አገልግሎት እና የድጋፍ አገልግሎት ዘርፎች ሠራተኞች የቅጥር ሁነታና አስተዳደር የሲቪል ሰርቪስ ሕጎች ተፋፃሚ ናቸው።[7]
የሙከራ ግዜ
በአዋጁ መሰረት የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኛ ቋሚ ሆኖ ከመቀጠሩ በፊት በካሪክለሙ መሰርት በዉጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ እንስቲትዩት የሚሰጠዉን የአንድ ዓመት የክፍል ዉስጥ የዲፕሎማቲክ ስልጠና እና ለአንድ አመት ተኩል የሚሰጠዉን የስራ ላይ ስልጠና በአጥጋቢ ዉጤት ማጠናቀቅ እንዳለበት ይደነግጋል።[8] እዚህ ነጥብ ላይ ከፌደራሉ ሲቪል ሰርቪስ አዋጅ የሚለይበት ዋናው ነጥቦች፡-
- የሙከራ ግዜው ርዝመትና
- የሙከራ ግዜው ዓላማ ናቸው።
በሲቪል ሰርቪስ አዋጅ የሙከራ ግዜ ስድስት ወር ሆኖ የሙከራ ግዜ ተቀጣሪው በተቀጠረበት የስራ መደብ ከኣጥጋቢ በታች ካመጣ የሙከራ ግዜው ለተጨማሪ ሦሥት ወር እንደሚራዘም ይገልፃል። የሙከራ ግዜው ዓላማም አዲስ የተቀጠረ የመንግስት ሰራተኛ ስለ ስራ አፈፃፀሙ ክትትል እየተደረገ ብቃቱን ለማረጋገጥ ነው።[9] በሌላ በኩል በዉጭ ግንኙነት አዋጅ የሙከራ ግዜ ሁለት ዓመት ተኩል ሆኖ ቢያንስ ኣጥጋቢ የስራ አፈፃፀም ምዘና ዉጤት ካላስመዘገበ የሙከራ ግዜው ለተጨማሪ ስድስት ወር እንደሚራዘም ይገልፃል። የአዋጁ አጠቃላይ ድንጋጌዎች በጥምረት ሲነበቡ የሙከራ ግዜው ዓላማ ከብቃት ምዘና በተጨማሪ የሙከራ ግዜ ተቀጣሪው አመለካከትንም ለመመዘን ጭምር ነው።[10] በዚህ ጉዳይ ሁለቱ አዋጆች የሚያመሳስላቸው በተራዘመው የሙከራ ግዜ፣ የሙከራ ግዜ ተቀጣሪው ከኣጥጋቢ በታች ካመጣ ያለ ካሳ መሰናበቱ ነው።
የተለማማጆች ሁኔታ
አዋጁ ሚኒስትሩ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በተቋማቱ ከፍተኛ ዉጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል በተለማማጅነት መመልመል እንደሚችል፣የሚለማመዱ ተለማማጆች ስለሚኖራቸው መብትና ግዴታ እንዲሁም የመመረቅያ ጥናቶቻቸው ከዉጭ ግንኙነት አገልግሎት ሥራ ጋር የሚዛመዱ እንዲሆኑለማበረታታት የተለያዩ ማትግያዎች ስለሚዘጋጁበት በመመሪያ እንደሚወሰን ይገልፃል።[11]
ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ተለማማጅ መሆን የሚችለው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመማር የሚገኝ ሲሆን የልምምድ ግዜዉም እስከሚመረቅ ያለዉን ግዜ ነው። በተጨማሪ የሚመለመሉት በተቋማቱ ከፍተኛ ዉጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል ሆኖ የሚመለመሉትም ሚኒስትሩ ከነኚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ነው። እዚህ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ፣ በተማሩባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከከፍተኛ ዉጤት በታች ያመጡ፣ ወይም በራሳቸው ተነሳሽነት ጥያቄ በማቅረብ ተለማማጅ መሆን ይችላሉ ወይ የሚሉ ናቸው። አዋጁ በማንበብ መረዳት እንደሚቻለው የሚመለምለው ሚኒስትሩ፣ የሚመለመሉትም ያልተመረቁ ከፍተኛ ዉጤት ያስመዘገቡ ናቸው።
ደሞዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች
የአሠሪ ዋና ዋና ግዴታዎች ከሚባሉት መካከል ደሞዝ የመክፈል ግዴታ ቀዳሚው ነው። የብዙ አገራት ልምድ እንደሚታየው በብዙ አገራት በተለያዩ ግዜያት በተለይም በኢንዱስትሪ አብዮት ግዜ እንደታየው በሠራተኛና አሰሪ መካከል ባለው ከፍተኛ የሆነ የመደራደር አቅም አለመመጣጠን(Bargaining Power) ሠራተኛው ላይ ከፍተኛ ለሆነ የጉልበት ብዝበዛ መጋለጣቸው ታሪክ ምስክር ነው። ይሄን ለመከላከልም በሁሉም አገራት(በተለይም በግል ዘርፋቸው) በሚያስብል መልኩ ዝቅተኛ የስራ ሁኔታዎች(Minimum Working Conditions) በማስቀመጥ መፍትሔ ሊሰጡት ሞክረዋል። አሰሪው መንግሥት በሚሆንበት ግዜ፣ መንግስት የዜጎቹን ደኅንነት መጠበቅና የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ግዴታው ስለሆነ ሠራተኛው ለጉልበት ብዝበዛ የመጋለጥ ዕድሉ “በጽንሰ-ሐሳብ ደረጃ” ዝቅተኛ ነው። ሕገ-መንግስቱም ሁሉም ኢትዮጵያዉያን የሀገሪቱ የተጠራቀመ ዕውቀትና ሀብት ተጠቃሚዎች የሚሆኑበትን መንገድ የመቀየስ፣ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች በማሻሻል እኩል ዕድል እንዲኖራቸው የማድረግ፣ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታ እንዳለበት ያስቀምጣል። በተጨማሪም፣ የሠራተኛዉን ህዝብ ጤንነት፣ ደህንነትና የኑሮ ደረጃ ለመጠበቅ መንግስት መጣር እንዳለበት ሕገ-መንግስቱ ይደነግጋል።
ሚኒስትሩ ከሚዘረጋው ሙያዊ የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት ሥርዓትና ከመንግስት የመክፈል አቅም ጋር በማገናዘብ፣ ተጨባጭ ብቃትና ችሎታ ያላቸዉን ባለሙያዎች ወደ ሚኒስቴሩ ለመሳብና ይዞ ለማቆየት የሚያስችል የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኞች የደሞዝ እርከን እና ተጨባጭ ዉጤትን መሠረት የሚያደርግ የማትግያ ሥርዓት አጥንቶ ለሚመለከተው የመንግስት አካል በማቅረብ፤ ሲፈቀድ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ተገልጿል።[12]
የሚከፈረለው የደሞዝ መጠን በዋናነት የሚወሰነው የአገሪቷ የመክፈል አቅም ነው፤ ትግራዎት ሲተርቱ “ዘየብላያ አዴኻስ ካብ እምኒ ትፀንዕ”[13] እንደሚሉት አገሪቷ የመክፈል አቅም ከሌላት ሌሎች አገራት እንደሚያደርጉት ተበድራ ለደሞዝ መክፈል ማዋል ትክክል አይደለም፤ መንግስት አንፃራዊ የሆነ የመክፈል አቅም ቢኖረዉም፣ የተገኘዉን በሙሉ ለፍጆታ ይዋል ማለትም አይደለም። ነገር ግን የአገር እድገት ያለ ህዝብ እድገት ትርጉም የሌለው በመሆነ የማመጣጠን እና እድገቱም ፍትኃዊና ሁሉን አቀፍ ማድረግ መቻል ነው።
የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኞች የደሞዝ እርከን እና ተጨባጭ ዉጤትን መሠረት የሚያደርግ የማትግያ ሥርዓት ከመንግስት የመክፈል አቅም ጋር በማገናዘብ፣ ተጨባጭ ብቃትና ችሎታ ያላቸዉን ባለሙያዎች ወደ ሚኒስቴሩ ለመሳብና ይዞ ለማቆየት የሚያስችል አጥንቶ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በማቅረብ እና በማስፈቀድ ተግባራዊ ማድረግ ነው። በአዋጁ መሰረት የሠራተኞች የደሞዝ እርከን እና የማትግያ ሥርዓት ተግባራዊ የሚሆነው ደንብ በማዉጣት ሳይሆን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን አጥንቶ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በማቅረብ እና በማስፈቀድ ነው።
የደረጃ እድገት
የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት የዲፕሎማቲክ፣ የአስተዳደርናአገልግሎት እንዲሁም የድጋፍ አገልግሎት በሚባሉ ሦሥት ዘርፎች የተከፈለ ነው።[14]የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ዘርፍ በበኩሉ ከፍተኛ፣ መካከለኛ፣ መጀመሪያ ደረጃ የአገልግሎት ምድብና የቆንስላ አገልግሎት ምድብ በመባል ይከፈላሉ። በዲፕሎማቲክ አገልግሎት ምድብ ከፍተኛው ባለሙሉ ስልጣን ሚኒስትር ሲሆን የመጨረሻው ደግሞ አታሼ ነው።[15]የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኛ የመነሻ ቅጥር ከአታሼ ደረጃ እንደሚጅምርም አዋጁ ይደነግጋል።[16]
ቋሚ የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኛ በትምህርትና በሙያው ክህሎት ዝግጅት፣ በሥራና ልምዱና የአፈፃፀም ምዘና ዉጤት ላይ ተመስርቶ ከአንድ የሙያ መሰላል ወደሚቀጥለው ከፍ ያለ የሙያ መሰላል በደረጃ እድገት የሚሸጋገርበትን ስርዓት ሚኒስቴሩ እንደሚዘረጋ፤ የላቀ የሥራ አፈፃፀም ምዘና ዉጤት የሚያስመዘግብ የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኛ በልዩ ሁኔታ ፈጣን የደረጃ እድገት የሚያገኝበት አሰራር በስርዓቱ እንደሚካተት ተገልጿል።[17] በምን ያክል ግዜ ልዩነት ከአንድ እርከን ወደ ሌላ እርከን እንደሚያድግ፣ ለማደግ የሚያስፈልጉ መስፈርቶች፣ እና በልዩ ሁኔታ ፈጣን የደረጃ እድገት የሚገኝበት አሰራርና አተገባበር ለመወሰን ረቂቅ ደንብ የተዘጋጀ ቢሆንም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከአንድ እርከን ወደ ሌላ እርከን ለማደግ የሚያስፈልገው ግዜ ረጅም ከመሆኑ የተነሳ ተጨባጭ ብቃትና ችሎታ ያላቸዉን ባለሙያዎች ወደ ሚኒስቴሩ ለመሳብና ይዞ ለማቆየት የሚደረገዉን ስራ ከባድ ያደርገዋል።
ምደባ፣ ጥሪና ዝዉዉር
በአዋጁ መሰረት አራት ዓይነት የምደባ፣ ጥሪና ዝዉዉር አካሄዶችና አንድ ለየት ያለ የምደባና ዝውውር ስርዓት ተቀምጧል። እነሱም፡-
- ከሚኒስቴሩ ወደ ሚስዮን
- ከሚስዮን ወደ ሚኒስቴሩ
- ከሚስዮን ወደ ሚስዮን እና
- በሚኒስቴሩ ዉስጥ ባሉ የስራ ዘርፎች መካከል ናቸው። በበይነ-መንግስታዊ ድርጅት ዉስጥ በግዝያዊነት ለማገልገል በሚኒስትሩ የሚሰጥ ይሁንታም ከዚህ ጉዳይ የተያያዘ ነው።[18]
ከሚኒስቴሩ ወደ ሚስዮን፣ ከሚስዮን ወደ ሚኒስቴሩ እና ከሚስዮን ወደ ሚስዮን የሚደረገው ምደባ፣ ጥሪና ዝዉዉር “የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኞች የዉጭ ምደባ፣ ዝዉዉርና ጥሪ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 17/2005” መሰረት ተግባራዊ ይሆናል። በዚህ መመሪያ ካሉት ክፍተቶች መካከል የዉጭ ምደባ ኮሚቴ አባላት ስብጥር ነው። በመመሪያው አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የኮሚቴው አባላት፡-
- የሰው ሀብት ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ጀኔራል……………………………ሰብሳቢ
- ከአምስቱ አህጉራት ዳይሬክቶሬት ጀኔራሎች በኮሞቴው የሚመረጥ አንድ-ም/ሰብሳቢ
- አምስቱም የአህጉራት ዳይሬክቶሬት ጀኔራሎች…………………………………..አባል
- የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ጀኔራል……………………………………………..አባል
- በሠራተኛው የሚመረጡ የሠራተኞች ተወካዮች……………………………….…አባል
- የሰው ሀብት ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ጀኔራል የሚመደብ……ፀሐፊ ድምጽ አልባ
እዚህ ላይ በኮሚቴው ያልተካተቱት ዳይሬክቶሬት ጀኔራሎች ማለትም፣ የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የቆንስላ ጉዳዮች፣ ቢዝነስ ዲፕሎማሲ፣ የዳያስፖራ ጉዳዮች፣ ድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች እና የፖሊሲ ምርምርና ትንተና ዲፓርትመንት ዳይሬክቶሬት ጀኔራሎች በኮሚቴው አለመካተት በምደባው ፍትሓዊነትና ሁሉን አቀፍነት የራሱ ተጽዕኖ አለው።
በዚህ ርእስ ላይ መነሳት ያለበት ሌላው ጉዳይ፣ በበይነ-መንግስታዊ ድርጅት ዉስጥ በጊዜያዊነት ወይም በዉሰት ማገልገል ስለሚቻልበት አገባብ ነው። አንድ የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት ሠራተኛ በበይነ-መንግስታዊ ድርጅት ዉስጥ ለኢትዮጵያ ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር ታይቶ በጊዜያዊነት እንዲያገለግል ሲፈለግ ወይም ሠራተኛው በራሱ ጥያቄ ሲያቀርብ ሚኒስትሩ ሊፈቅድ እንደሚችል፤ የሚኒስትሩ ይሁንታ ሳያገኝ በበይነ-መንግስታዊ ድርጅት ዉስጥ ሊያገለግል እንደማይችል በአዋጁ ተገልጿል። በተጨማሪ በበይነ-መንግስታዊ ድርጅት ዉስጥ በጊዜያዊነት ወይም በዉሰት እንዲያገለግል የሚሰጠው ፈቃድ በበይነ-መንግስታዊ ድርጅቱ ዉስጥ በጊዜያዊነት ወይም በዉሰት ማገልገሉ በዋናነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚኖረው ፋይዳ ሲኖር ነው። አሁን ባለው አካሄድ ግን አዋጁ በሚያስቀምጠው ግልፅ፣የተቀናጀና ወጥነት ያለው አሰራር አልተዘረጋም።
የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ ተፈፃሚነት
አግባብነት ያላቸው እና የማይቃረኑ የፌደራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/1999 እና በዚሁ አዋጅ መሠረት የወጡ ደንቦችና መመሪያዎች እንዲሁም የሌሎች ሕጎች ድንጋጌዎች በዚህ አዋጅና በአዋጅ መሠረት የወጡ ደንቦችና መመሪያዎች የተሸፈኑ ጉዳዮችን በሚመለከት በሟሟያነት ተፈፃሚ እንደሚሆኑ አዋጁ ይደነግጋል[19]። ነገር ግን በሕግ አረቃቀቅ ስርዓት(Legislative Drafting) የአዋጁ የተፈፃሚነት ወሰን ከተቀመጠ በኃላ የሌሎች ሕጎች ድንጋጌዎች በአዋጁ ባልተሸፈኑ ጉዳዮች ተፈፃሚነት ክፍተት የመሙላት ሚና ይኖራቸዋል። ይህ አዋጅ ስናየው ግን የተፈፃሚነት ወሰን ካለመኖሩ በተጨማሪ የሌሎች ሕጎች ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የሚኖራቸው በዚህ አዋጅና አዋጁን መሠረት አድርገው የወጡ ደንቦችና መመሪያዎች የተሸፈኑ ጉዳዮችን በሚመለከት በሟሟያነት እንደሚያገለግሉ ነው። በዚህ አዋጅ ያልተሸፈኑ በሲቪል ሰርቪሱ አዋጅ እና የሌሎች ሕጎች ድንጋጌዎች የተሸፈኑ ጉዳዮች ቢሆኑም በአዋጁ አተረጓጎም ተፈፃሚነት አይኖራቸዉም። ስለዚህ የድንጋጌው አላማ የሲቪል ሰርቪሱ አዋጅ እና የሌሎች ሕጎች ድንጋጌዎች የዉጭ ግንኙነት አዋጅ ዉስጥ በተሸፈኑ ጉዳዮች ያልተገለፀ ዝርዝር ካለ እንደማሟያ እንዲያገለግሉ ነው ማለት ይቻላል።
እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ፣ የዉጭ ግንኙነት አዋጁ በዲፐሎማቲክ አገልግሎት ዘርፍ የሚሰራ የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኛ በመግብያው ላይ እንደተቀመጠው …ወጥነት ባለዉና በተቀናጀ ተቋማዊ አሰራር ለማስተዳደር…የሚያስችል መሆን ስላለበት ሁሉን አቀፍ እና ሰራተኛዉም የተቋሙ ዋናው ሀብት በመሆኑ በዋናነት የሠራተኛው መብትና ግዴታዎች በአዋጁ ማካተት ወይም የሚካተቱበት አገባብ መቀመጥ ነበረበት። ለምሳሌ በአዋጁ ያልተገለፁ
- መደበኛ የስራ ሰዓት፣
- የስራ መዉጫና መግብያ ሰዓት፣
- የትርፍ ሰዓት ስራ፣
- ስለ ሕዝብ በዓላትና የሳምንት የስራ ቀናት
- የዓመት ዕረፍት ፈቃድ
- የወሊድ ፈቃድ
- የሕመም ፈቃድ
- በሥራ ላይ ስለሚደርስ ጉዳት
- ስልጠና
- የግል ማኅደር
- የዲስፕሊን ቅጣት
- የስራ ዉል ስለማቋረጥ የተመለከቱ እና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች በየትኛው ሕግ እንደሚተዳደሩ ግልፅ አይደለም።
የአዋጁ እና በአፈፃፀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶች
አሁን አዋጁ በደንብ መተግበር ባልተጀመረበት ሁኔታ ያሉበትን ክፍተቶች ቡሉ በሙሉ ለመዘርዘር አስቸጋሪ ቢሆንም፤ አዋጁ በሚፈለገው መልኩ አለመተግበር ምክንያት በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራ አለመሰራት፣ የአዋጁ ይዘት አለማወቅ ወይም ለመተግበር አለመፈለግ ቢሆኑ እንኳ በከፊል የአስተዳደር ድክመት ነው። በአዋጁ ላይ አሰራር እንደሚዘረጋላቸው የተቀመጡ ተግባራት ቢኖሩም እስካሁን አሰራር አልተዘረጋላቸዉም። ከዚህ ጥናት ጋር የተያያዘ በአዋጁ እና በአፈፃፀም ላይ ካሉ ክፍተቶች መካካል፡-
- የመሸጋገሪያ ድንጋጌ አለመኖር፡- አብዛኛዎቹ ስርዓት የሚቀይሩ አዋጆች ሲወጡ፣ ማለትም መስሪያ ቤቱ ሲተዳደርበት የነበረው ሕግ ሲቀየር፣ የነበረው ተቋም በአዲስ ተቋም ሲቀየር፣ የተለየ መብትና ግዴታ የሚጥል ሕግ ሲወጣ ከነበረው አሰራር ወደ አዲስ አሰራር ለመግባት የሽግግር ግዜ ያስፈልጋል። በተያያዘ ጉዳይ በነባሩ አዋጅና በአዲሱ አዋጅ ያሉ መብትና ግዴታዎች አለመመሳሰል የነበሩ መብትና ግዴታዎች ወደ አዲሱ አዋጅ እንዴት እንደሚተላለፉ፣ የተጀመሩ ጉዳዮች እንዴት እንደሚስተናገዱ፣ በነባሩ ሕግ የነበሩ ደረጃዎች በአዲሱ ሕግ እኩያዎቹ ማሳየት ያካትታል። ለምሳሌ፡- በሲቪል ሰርቪሱ አዋጅ ቅጥር የሚፈፀመው በፕሳ ስርዓት ሆኖ ከፕሳ1 እስከ ፕሳ9 የሚደርስ ነው 9 ደረጃዎች አሉት፤ በዉጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ ደግሞ ከአታሼ ጀምሮ እሰከ ባለሙሉ ስልጣን ሚኒስትር የተዘረጋ በአጠቃላይ 10 ደረጃዎች አሉት። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ በሲቪል ሰርቪሱ አዋጅ ፕሳ1 የነበረ ሰው በዉጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ እኩያው አታሼ ነው ወይስ ሦሥተኛ ፀሐፊ፣ በሲቪል ሰርቪሱ አዋጅ ፕሳ9 የነበረ ሰው በዉጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ እኩያው ሚኒስትር ነው ወይስ ባለሙሉ ስልጣን ሚኒስትር? የሚሉ ናቸው። በነባሩ አዋጅ የነበሩትን ደረጃዎች በአዲሱ አዋጅ ያላቸዉን ምንዛሪ በኣዋጁ መገለፅ ነበረባቸው። እንደ መፍትሔ ግን አዋጁን ለማስፈፀም በሚወጣው ደንብ ማካተት ይቻላል።
- የአቀጣጠር መንገድ፡- የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኛ የመነሻ ቅጥር ከአታሼ እንደሚጀምር፤ ከአታሼ በላይ ያሉ ክፍት የስራ ቦታዎች በደረጃ እድገት ወይም በዉስጥ ዝውዉር እንደሚሞላ ይደነግጋል።[20] ከአታሼ በላይ ያሉ ክፍት የስራ ቦታዎች በደረጃ እድገት ወይም በዉስጥ ዝውዉር መሙላት ካልተቻለ ሚኒስቴሩ በሥራ አመራር ምክር ቤት ዉሳኔ በዚህ አዋጅ የተደነገጉ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሠራተኞችን በመቅጠር ሊሞላ እንደሚችል ይደነግጋል። እዚህ ላይ የሚታየው ክፍተት ክፍት በሆኑ የስራ ቦታዎች የሚቀጠሩ የዉጭ ሠራተኞች ከመቀጠሩ በፊት በደረጃ እድገት ወይም በዉስጥ ዝውዉር ለመሙላት ተሞክሯል ወይ፣ በዚህ አዋጅ የተደነገጉ መስፈርቶችን ያሟላሉ ወይ፣ቅጥር የተፈፀመው በሥራ አመራር ምክር ቤት ዉሳኔ ነው እና ከዉጭ እንዲቀጠሩ ለዉሳኔ የሚቀርቡ ሠራተኞችስ እንዴት ነው የሚመለመሉት(በትዉውቅ ነው ወይስ በታዋቂነት) የሚሉ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው። ለምሳሌ አንድ በሚኒስትር አማካሪ 1 የሚቀጠር የዉጭ ሠራተኛ ደንቡ ገና ረቂቅ ቢሆንም ቢያንስ 15 ዓመት የስራ ልምድ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ግልፅ የሆነ የስራ ማስታወቅያ ወጥቶ፣ መግቢያ ፈተና አልፈዉ፣ በአዋጁ ያሉትን ሌሎች መስፈርቶች አሟልቶው ሲገኙ እና የሥራ አመራር ምክር ቤቱ ሲወስን ብቻ ነው ቅጥር ሊፈፀም የሚችለው። አሁን ባለው አካሄድ ግን አሰራሩ በግለሰቦች ይሁንታ የተመሰረተ እንጂ ወጥ የሆነ ስርዓት የተዘረጋለት ግልፅነትና ተጠያቂነት የተላበሰ አሰራር አይደለም። ግልፅ የሆነ ሕግ ባለበት ሁኔታ ከተቀመጠው ሕግ ዉጪ መስራት በተዘዋዋሪ መልኩ ሕጉን እንደመሻርና እንደማሻሻል ስለሚቆጠር ዉሳኔ የሰጠው አካል ማንም ሰው ይሁን አሰራሩ ትክክል አይደለም።
- የተለማማጆች ሁኔታ፡- አዋጁ ሚኒስትሩ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በተቋማቱ ከፍተኛ ዉጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል በተለማማጅነት መመልመል እንደሚችል፣የሚለማመዱ ተለማማጆች ስለሚኖራቸው መብትና ግዴታ እንዲሁም የመመረቅያ ጥናቶቻቸው ከዉጭ ግንኙነት አገልግሎት ሥራ ጋር የሚዛመዱ እንዲሆኑ ለማበረታታት የተለያዩ ማትግያዎች ስለሚዘጋጁበት በመመሪያ እንደሚወሰን ይገልፃል። አሁን ባለው አሰራር ግን መመሪያ ካለመዉጣቱም በተጨማሪ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተመረቁ በኃላ ላስመዘገቡት ዉጤት ትኩረት ሳይሰጠው በተለማማጅነት እየገቡ ይገኛል። በተለማማጅነት የሚገቡትም ተለማማጅ ሆኖ ለመቀጠል ሳይሆን በጊዜ ሂደት ወደ ዲፕሎማቲክ አገልግሎት ቋሚ ሠራተኝነት ሲለሚሸጋገሩ ነው። ይሄ ማለት ግን ከተመረቁም በኃላ በተለማማጅንት አይግቡ ሳይሆን መመሪያ ተዘጋጅቶለት ግልፅ፣ ተአማኒና ያለው፣ ግልፀነትና ከወገንተኝነት የፀዳ መሆን አለበት።
- የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ ተፈፃሚነት፡- በዚህ አዋጅና በአዋጅ መሠረት የወጡ ደንቦችና መመሪያዎች የተሸፈኑ ጉዳዮችን በሚመለከት አግባብነት ያላቸው እና የማይቃረኑ የፌደራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/1999 እና በዚሁ አዋጅ መሠረት የወጡ ደንቦችና መመሪያዎች እንዲሁም የሌሎች ሕጎች ድንጋጌዎች በሟሟያነት ተፈፃሚ እንደሚሆኑ አዋጁ ቢደነግግም በዚህ አዋጅ ያልተሸፈኑ በሲቪል ሰርቪሱ አዋጅ እና የሌሎች ሕጎች ድንጋጌዎች የተሸፈኑ ጉዳዮች ቢሆኑም በአዋጁ አተረጓጎም ተፈፃሚነት አይኖራቸዉም። አግባብነት ያላቸው እና የማይቃረኑ የፌደራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/1999 እና በዚሁ አዋጅ መሠረት የወጡ ደንቦችና መመሪያዎች እንዲሁም የሌሎች ሕጎች ድንጋጌዎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ የተሸፈኑ የሚለዉን የቃል ግድፈት ስለሆነ ያልተሸፈኑ በሚለው መስተካከል አለበት።
የዉጭ ግንኙነት አገልግሎት ሥራዎች ግልፅ፣ ቀልጣፋና ዉጤታማ በሆነ መንገድ ለመምራት እና ተጨባጭ ብቃትና ችሎታ ያላቸዉን ባለሙያዎች ወደ ሚኒስቴሩ በመሳብና ይዞ በማቆየት የዉጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው ያስቀመጣቸውን ግቦች በተሟላ መልኩ ለማሳካት፣ ሙያዊ የዲፕሎማሲ ሥርዓት(Career Diplomatic Service) በመተግበር፣ የማስፈፀም አቅሙ፣ ብቃቱና ክህሎቱ የዳበረና አገራዊ ተልዕኮዉን በሚገባ የሚወጣ የሰው ሀይል ለማፍራትና ለማስተዳደር፣ በዳሰሳ ፅሑፉ የተገለፁትን እና ሌሎች በስራ ላይ ያሉ አጠቃላይ ሕጎች በተለይም በዉጭ ግንኙነት አዋጁ ያሉትን ክፍተቶች እና በአተገባበራቸው ላይ የሚታዩ ከአዋጁ ይዘት የማይጣጣሙ አሰራሮች በማስተካከል የዉጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው ያስቀመጣቸውን ግቦች በተሟላ መልኩ በማሳካት የአገራችን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ አለብን።
[1] the Constitution of the Federal Democratic Republic of Ethiopia Proclamation No. 1/1995, Federal Negarit Gazeta , 1st year No.1, Addis Ababa, 21st August 1995 አንቀፅ 89 እንዲሁም 41 እና 42
[2] Foreign Service Proclamation No. 790/2013, Federal Negarit Gazeta , 19th year No.52, Addis Ababa, 23rd July, 2013 አንቀጽ 2(1)፣ 2(2)፣ 2(10) እና 2(11) ማንበብ ይቻላል።
[3] የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል እና የፖሊሲ ምርምርና ትንተና ዲፓርትመንት ዳይሬክተር የሆኑትን እንደቅደም ተከተላቸው ኃይለስላሴ ሱባና አምባሳደር መርዋን በድሪ በመጠየቅ ያገኘሁት ነው።
[4] Supra note 2 አንቀጽ 21
[5] Id አንቀጽ 22
[6] Id አንቀጽ 2(22) እና 24(2)
[7] Id አንቀጽ 21(3)
[8] Id አንቀጽ 25(3)
[9] Federal Civil Service Proclamation No. 515/2007, Federal Negarit Gazeta , 13th year No.15, Addis Ababa, 19th February, 2007 አንቀጽ 20(1) 20(2)፣ እና 20(3) ማንበብ ይቻላል።
[10] Supra note 2 አንቀጽ 25(3) እና 25(4)
[11] Id አንቀጽ 31
[12] Id አንቀጽ 32
[13] እናት ከሌላት ልቧ ከድንጋይ በላይ ይጠጥራል ማለት ነው።
[14] Id አንቀጽ 7
[15] Id አንቀጽ 8፣9፣10 እና 11 ይመለከቷል።
[16] Id አንቀጽ 23(2)
[17] Id አንቀጽ 27 (1) እና (2)
[18] Id አንቀጽ 29፣ 33 እና 36 ይመለከቷል።
[19] Id አንቀጽ 57(1)ና (2) አጽንኦት ተጨምሮበት
[20] Id አንቀጽ 23(2) እና (3)