በነመንግስቱ ኃይለማርያም በቀረበ ክስ የነበረው የሕግ ክርክር

የ”ጊዝያዊ” ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ወይም መንግስት፣ የደርጉ ጠቅላላ ጉባኤና የቋሚ ኮሚቴው ሊቀ-መንበር ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ጨምሮ 106 ተከሳሾች የተካተቱበት በዋነኝነት ዘርን በማጥፋት፣ በሰብአዊ ፍጥረት ላይ ስለተፈፀመ ወንጀል በሚል በቀረበው ክስ ላይ፣ ከመስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ጀምሮ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ወይም መንግስት አቋቁመው በጠቅላላ ጉባኤ በቋሚ ኮሞቴና ንዑሳን ኮሚቴነት ተዋቅረው ሀገሪቷን በጋራና በብቸኝነት ሲያስተዳድሩ ወንጀል ለመስራት ተስማምተው በግብረ አበርነት በ1949 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቅጥር 281 የተመለከተውን ዘርን የማጥፋት ወንጀል ፀረ ሕዝብና ፀረ አብዮት ባሏቸው የተለያዩ የፖለቲካ ቡድን አባላት ላይ በመፈፀም፤ እንዲፈፀም በማድረግና አፈፃፀማቸውን ለመርዳት የተለያዩ ከፍተኛና የቀበሌ መሪዎች፣ አብዮት ጠባቂዎችን፣ ካድሬዎችን በአጠቃላይ እነሱ እየመለመሉ መሣሪያ ያስታጠቋቸው አብዮታዊ ጓዶች ያሏቸውን ሁሉ በመሰብሰብያ አዳራሾች፣ ሜዳዎች በመገናኛ ብዙኃን መሣሪያዎች እየተጠቀሙ የፖለቲካ ቡድኑ አባላት ስም በመጥራት እንዲደመሰሱ ከ1967 እስከ 1975ዓ.ም. ባሉት የተለያዩ ወራትና ቀናት በንግግር፣ በስዕልና በፅሑፍ በአዲስ አበባ ከተማና በመላው አገሪቷ በማነሳሳት በማደፋፈራቸውና በሌላ መዝገብ ክስ የሚቀርብባቸው ተከሳሾችም በሺዎች የሚቀጠሩ የተለያዩ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኑን አባላት በመግደላቸው በ1949 ዓ.ም. በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በቅጥር32/1/ሀ እና 286/ሀ የተመለከተውን ተላልፈው ወንጀል ፈፅመው በመገኘታቸው እንደተከሰሱ ይገልፃል።
ተከሳሾች በዋነኝነት ካቀረቧቸው የጋራ መከላከያዎች መካከል፡-
1. ደርግ የፈፀማቸው ተግባራት በሕግ የተፈቀዱ ናቸው፤ በ1949 ዓ.ም. የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በእግድ(Suspension) የቆየ በመሆኑ ተፈፃሚ መሆን የለበትም እና
2. የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቅጣት የወጣ ኮንቬንሽን ውስጥ የፖለቲካ ቡድንን ለይቶ በከፊል ወይም በሙሉ ማጥፋት የዘር ማጥፋት የሚል አያካትትም የሚሉ ናቸው።
የ”ጊዝያዊ” ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ወይም መንግስት ይፈፅማቸው የነበሩትን ድርጊቶች በግዜው በሚያወጣቸው ሕጎች መሰረት በማድረግ የሚፈፀሙ ስለነበሩ፣ ማለትም፡-
አዋጅ ቁጥር 1/67 ደርግ የተቋቋመበት አዋጅ
አዋጅ ቁጥር 110/69 በፀረ አብዮቶኞች እርምጃ የመውሰድ ስልጣን
አዋጅ ቁጥር 129/69 የተለያዩ አካላት ያሉት የዘመቻ መምሪያ ማቋቋምያ
አዋጅ ቁጥር 129/69 ቁ.8/3 ፀረ አንድነትና ፀረ አብዮት ኃይሎችን ለመደምሰስ የወጣ አዋጅ መሰረት በማድረግ እርምጃ ይወሰድ ስለነበር፣ ደርግ የፈፀማቸው ተግባራት በሕግ የተፈቀዱ ናቸው የሚል መከራከርያ ቀርቧል።
በተጨማሪ በ1949 ዓ.ም. የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በእግድ(Suspend) የቆየ በመሆኑ ተፈፃሚ መሆን የለበትም በሚለው ጭብጥ ላይ የደርግ መንግስት የኢትዮጵያ ሕጋዊ መንግስት እንደነበረና የወሰዳቸው እርምጃዎች፣ የሰጣቸው ውሳኔዎችና ትእዛዞች ሕጋዊ እንደነበሩ፣ እንዲሁም በየግዜው ያወጣቸው አዋጆች ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና የሚያመጡ አንድነቷን የሚያስጠብቁ እንጂ ተቃዋሚዎችን ለመደምሰስ እንዳልነበረ፤ ደርግ የተቋቋመው ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተደረገበት ተፅእኖ ስለሆነ ወንጀል ለመፈፀም ወይም ዘር ማጥፋት ለመፈፀም ሀሳብ ያልነበረው መሆኑ እና ከተቋቋመ በኃላ የነበረውን ዓላማ በየግዜው እንደገለፀው የሕዝቡን ጥያቄ ለሟሟላት፣ ኢትዮጵያን ለማስቀደም እና ሕዝቡ የራሱ ገዢ እንዲሆን ማድረግ እንጂ ሥልጣን ለመያዝ ዘር ለማጥፋት ይሁን ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት እንዳልነበረ ተነስቷል።
የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቅጣት የወጣ ኮንቬንሽን ውስጥ የፖለቲካ ቡድንን ለይቶ በከፊል ወይም በሙሉ ማጥፋት የዘር ማጥፋት የሚል አያካትትም በሚለው መከራከሪያ፣ የተባበሩት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እ.ኤ.አ. 1945-1995 ባወጣው መግለጫ በቀረበው ሠነድ ቁጥር 102 ላይ የፖለቲካ ቡድኖች ልክ እንደ አንድ የሀይማኖት ብድን ታይተው ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ለምሳሌ ያክል በናዚ ዘመን አንድ የፖለቲካ ቡድንን ለይቶ ለማጥፋት፣ በርዕዮተዓለም ትግል ውስጥም እንደዚሁ የፖለቲካ ቡድን ኢላማ የማድረግ ሁኔታዎች የተስተዋሉ ስለሆነ ለፖለቲካ ቡድን ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ የተነሳ ሲሆን ከብዙ ክርክር በኃላ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ሳይቀበለው ቀርቷል። የተሰጠው ምክንያትም የፖለቲካ ቡድን የሚመሰርቱ አባላት ቋሚ ወይም የረጉ ስለማይሆኑ ማለትም መሠረታቸው የአባላቶቻቸው የፍላጎት እንቅስቃሴ እንጂ የቡድኑ ምርጫ ባለመሆኑ፣ ከዚህም በተጨማሪ የፖለቲካ ቡድንን በዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ማካተት የተባበሩት መንግስታት በአገሮች የውስጥ ትግል ጣልቃ እንደመግባት ስለሚቆጥሩት ኮንቬንስኑን ወይንም ዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት የሚቀበሉትን አገሮች ቁጥር ይቀንሳል፤ ብዙ አባል አገሮች ላይቀበሉት ይችላሉ፤ አንድ መንግስትም ራሱን ለመከላከል ችግር ሊፈጥርበት ይችላል በማለት ተቀባይነት ማጣቱ በመግለፅ ተከራክሯል።
የተነሱ መከራከርያዎች ሲታዩ፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በተለይም ደግሞ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች በመርህ ደረጃ የብዙ ወገኖች ፍላጎት ማሟላት ስላለባቸው፣ የሚደነግጓቸው የመብት ጥበቃዎች የቢያንስ ጥበቃዎች(Minimum Treshold) ሲሆኑ፣ አባል አገራት ለዜጎቻቸው የሚሰጡት የመብት ጥበቃም ቢያንስ አባል በሆኑባቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች የተገለፁትን በማክበር፤ እንዲሁም በውስጥ ሕጎቻቸው የመብቶቹ ይዘትና ጥበቃ ሊያሰፉት ይችላሉ። የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቅጣት የወጣው ኮንቬንሽን ውስጥ የፖለቲካ ቡድንን ለይቶ በከፊል ወይም በሙሉ ማጥፋት የዘር ማጥፋት ነው በሚል ባያካትተውም፣ አባል አገራት በውስጥ ሕጎቻቸው ሊያሰፉት እንደሚችሉ ግልፅ ነው፤ አገራችንም በ1949 ዓ.ም. በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ያደረገችው ይህንኑ ነው። የ”ጊዝያዊ” ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ወይም መንግስት ይፈፅማቸው የነበሩትን ድርጊቶች በግዜው በሚያወጣቸው ሕጎች መሰረት በማድረግ የሚፈፀሙ ስለነበሩ ተከሳሾች ጥፋተኛ መባል የለባቸውም በሚል በተነሳው ጉዳይ፣ እ.ኤ.አ. በ1969 የወጣው የቪየና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሰነድ(Vienna Convention on the law of treaties) አንቀጽ 27 መሰረት፣ አንድ አገር በአለም አቀፍ ስምምነቶች የሚጣሉባትን ግዴታዎች ላለመፈፀም የውስጥ ሕግ እንደ ምክንያት ማቅረብ እንደማይቻል ይደነግጋል። በሥነ-ሕግ(Jurisprudence) እይታም አንድ ሕግ እንደ ሕግ ተቀባይነት የሚኖረው ቢያንስ መሰረታዊ የሆኑ የዜጎች መብት ማክበር ሲችል ነው። እንዲሁም አንድ መንግስት የዜጎቹን መብት ለማፈን ሕግ ቢያወጣ እና ድርጊቱን የፈፀምኩት ሕግን በተከተለ መንገድ ነው ማለት ከሕግ መርህና ዓላማ አብሮ የሚሄድ አይደለም። የተፈጥሮ ሕግ ንድፈ ሓሳብ(Natural Law Theory) አቀንቃኝ የነበረ St. Thomas Aquinas እንዳለው ፍትሓዊነት የሚጎድለው ሕግ፣ ሕግ አይደለም(Lex iniusta non est lex(An unjust law is no law at all)) እንዳለው የ”ጊዝያዊ” ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ወይም መንግስት ይፈፅማቸው የነበሩትን ድርጊቶች የሕግ ካባ ለማልበስ እና የደርጉ የፖለቲካ ንቅናቄ ትክክል አይደለም፤ መገታት አለበት በሚል እምነት ዙርያ የተሰባሰቡ ወይም ይህን እምነት የሚከተሉ ወገኖችን የመደምሰስ ሐሳብ ይዞ በመነሳት በግዜው ያወጣቸው ሕጎች ለተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደ ሽፋን የሚያገለግሉ ናቸው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s