የምርጫ ወጪ ለመቆጠብ እና የክልላዊ መንግስታት ምርጫ ከአገራዊ ምርጫ በተጣጣመ መልኩ ለማስኬድ፣ በ2ቱ ደረጃዎች የሚካሄዱ ምርጫዎች በተመሳሳይ ጊዜ በየ5 ዓመቱ እንደሚካሄዱ ይታወቃል፡፡ (የፌዴራል እና ክልላዊ መንግስታት የስልጣን ቆይታ በተመሳሳይ ጊዜ የሚያበቃ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡)
የሕግ መሰረት
ከምርጫ እንዲሁም ከመንግስት እና ሕገ -መንግስታዊ ስርዓት ጋር በተያያዘ ተያያዥነት ያላቸው አንቀፆች፡- ዓንቀፅ 54፣ 56፣ 72ን 73 ናቸው፡፡ በሕገ – መንግስት ዓንቀፅ 54 ንኡስ ዓንቀፅ 1 መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ በቀጥታ፣ ሁሉን ባካተተና በሚስጥር የድምፅ መስጫ በሚደረግ ምርጫ በየ5 ዓመቱ እንደሚመረጡ ይደነግጋል፡፡ በተመሳሳይ፣ የመንግሥት (Government) ማቋቋምን በተመለከተ በምክር ቤቱ አብላጫ ወንበር ያገኘ ድርጅት ወይም የድርጅቶች ጥምር መንግስት በመመስረት የፌዴራል መንግስት እንደሚመሩ ይገልፃል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆን እንዳለበት፣ በምክር ቤቱ አብላጫ ወንበር ካገኘ ድርጅት ወይም የድርጅቶች ጥምር መንግስት እንደሚሆን፣ እንዲሁም የስልጣን ዘመኑ እንደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5 ዓመት እንደሚሆን ዓንቀፅ 73 ንኡስ ዓንቀፅ 1ና 2፣ እንዲሁም ዓንቀፅ 72 ንኡስ ዓንቀፅ 3 ይደነግጋሉ።
በዚህ መሰረት የኢፌዴሪ ሕገ – መንግስት ሲረቀቅ አገራችን የነበረችበትን ሁኔታና ያሳለፈችውን ታሪክ ግምት ውስጥ በማስገባት ምርጫ በታቀደለት ጊዜ ማካሄድ ለምርጫ የማይገባ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አፅኦት በመስጠት፣ ሕገ – መንግስቱ ስለ ምርጫ መራዘም በተመለከተ በሩን ዝግ ማድረጉ መረዳት ይቻላል፡፡
ከዚህ በተጫማሪ በሕገ -መንግስቱ ዓንቀፅ 9 ንኡስ ዓንቀፅ 4 መሰረት አገራችን የተቀበለቻቻው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገራችን የህግ አካል እንደሚሆኑ በተቀመጠው መሰረት፣ የአፍሪካ ዴሞክራሲ፣ ምርጫና አስተዳደር ቻርተር (African Charter on Democracy, Election and Governance) አገራችን ከተቀበለቻቸው ስምምነቶች በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ በቻርተሩ መሰረት አባል አገሮች ግዜውን የጠበቀ፣ ግልፅ፣ ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ ማካሄድ[1]፣ በፓለቲካ አደረጃጀታቸው የሕገ – መንግሥት የበላይነት ማስረፅ[2] (entrench the principle of the supremacy of the constitution in the political organization of the State)፣ ግዜውን የጠበቀ፣ ግልፅ፣ ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ ሲያካሂዱ የአፍሪካ ሕብረት የዴሞክራሲያዊ ምርጫ አስተዳደር መርሆዎች (African Union’s Declaration on the Principles Governing Democratic Elections in Africa) ለመተግበር ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያረጋግጡ[3]፣ እንዲሁም ሕጋዊ በሆኑ መንገድ ለተመረጡ የክልላዊ መንግስታት ስልጣናቸውን ማካፈል እንዳለባቸው[4] ይደነግጋል።
የፖለቲካ ግምገማ
የሕግ መሰረቱ ከላይ የተገለፀው ሲሆን፣ አስተማማኝ ሰላም አለመኖሩ፣ ወደ መደበኛ መኖሪያ ቦታቸው እና ዕለታዊ እንቅስቃሴያቸው ያልተመለሱ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖር፣ እንዲሁም አገራዊ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ አለመከናወኑ፣ የ2012 ዓ.ም. አገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በተቀመጠለት የጊዜ ሠሌዳ መካሄድ የለበትም የሚሉ ሃሳቦች ይንፀባረቃሉ፡፡
አገራዊ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ አለመካሄድ በምርጫው ጋር ያለው ግንኙነት በዋነኝነት አንድ የምርጫ ጣብያ ምን ያክል ህዝብ መሸፈን አለበት የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በመሆኑ፣ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ባይካሄድም እንደሚከተለው ተቀራራቢ ስሌት በመጠቀም እንደሚከተለው ማስላት ይቻላል፡፡ አጠቃላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ብዛት 550 ሲሆን፣ 20 ወንበር “በህዝብ ብዛት አነስተኛ ለሆኑ ብሔረሰቦች” የተደለደለ ነው፡፡ በዚህ መሰረት አጠቃላይ የህዝብ ብዛት (110 ሚልዮን) ለተቀረው 530 ወንበር በማካፈል፣ 1 የምርጫ ጠብያ 200000 ህዝብ ባለበት ማካሄድ ይቻላል፡፡
ማጠቃለያ
የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና በተለያዩ የአገሪቷ አከባቢዎች ላይ የሚስተዋሉትን
አለመረጋጋቶች በተመለከተም የመፈናቀሎቹ እና ያለመረጋጋቱ ዋነኛ ምክንያት ፖለቲካዊ እንድምታ ያላቸው በመሆኑ ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው
ናቸው፡፡ ምርጫው ማራዘም ችግሮቹን የበለጠ እንዲሰፉ እና እንዲወሳሰቡ በማድረግ ወደ የማንወጣው ውስብስብና ተመጋጋቢ ፖለቲካዊ፣
ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ቀውስ የሚያስገባን በመሆኑ፣ ያሉብንን ችግሮች ግን ለጎን መፍትሔ እየሰጠን ሕገ – መንግስቱ እና አገራችን
የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በሚያስቀምጡት መሰረት ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ ለምርጫ መቅረብ የሌለበት የህልውና
ጉዳይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
[1] Article 3 sub – Article 4 of African Charter on Democracy, Election and Governance
[2] Id Article 10 sub- article 1
[3] Id Article 17
[4] Id Article 34